ለወትሮው በቀላሉ የማዝን አይነት አይደለሁም፡፡ ዛሬ ግን በአይኔ የገባ ትዕይንት ልቤ ጋር ሲደርስ ሀዘን ፈጥሮ፤ ሀዘኑ የውስጥ እግሬን እንኳ ሲዘልቀው ይሰማኛል፡፡ ጁምዓ ሚያዝያ 22/2002 ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገደማ ከሰላት መልስ በፍጥነት ኀ/ጊዮርሲስ ከሚገኘው ኩርቱ ህንፃ ላይ ስወጣ አራተኛው ፎቅ ላይ ሆኜ ያየሁትና የውስጥ እግሬን ተሰማኝ ያልኳችሁ ትዕይንት ተጨማሪ እርምጃ እንዳልሄድ ይዞኛል፡፡
ከመሬቱ 14 ሜትር ገደማ ርቄ የማያቸው ድቅቅ ያሉ ፍጥረታት ከአንዋርና ከበኒ መስጂድ የሚወጡ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ከላይ ሆናችሁ ስታዩት ንፋስ የሚያወዛውዘው የጥጥ እርሻ ነው የሚመስለው፡፡ ሁካታ የለችም፡፡ ሁሉም በአርምሞ (በፀጥታ) ወደየቤቱ ሲጓዝ በዛ ፀጥታ ሥር ኃያል ጩኸት ተሰማኝ፡፡ ኡኡታ፡፡ የዝምታ ሁካታ፡፡
እንደዚያ ድቅቅ ያለ ሆኖ ከሚታየኝ ሕዝብ ውስጥ አድማሱን የሚታከክ ትልቅ፣ ት..ል..ቅ ማንነት ጎልቶ ይታየኛል፡፡ ለእኔ ብሶና ገዝፎ የታየኝ(የተሰማኝ) ግን፤ አስፈሪ ጩኸት ነው፡፡ ያ ሁሉ ሕዝብ ከአንድ ቦታ ተነስቶ በየፊናው ሲበተን፣ ንግሥቲቱ እንደጠፋችው ንብ ሆኖ ተሰማኝ-አባት አልባነት፡፡ በዛ ርጋታ መሃል ችኮላ ይታየኛል፡፡ እንዲህ በእውን የማያው ምስል ሌላ ትርጉም እየሰጠኝ ሳስብ (ስቆዝም ብል ይሻላል) አስፋልቱን ሰዎች ለቀውት መኪኖች ተረከቡት፡፡
• * *
መሪ በኢስላም ትልቅ ቦታ አለው፡፡ መሪን (አሚርን) መታዘዝ ከኢስላም ጠንካራ አቋሞች አንዱ ነው፡፡ ሙስሊሞች የትም ብንሆን መሪ ይኖረናል፡፡ ታላቁ ነቢይ የፍጥረታት አለቃ፣ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ)፣ሦስት ሰዎች እንኳ መንገድ ሲሄዱ አንዱን መሪ (አሚር) እንዲያደርጉት አዘዋል፡፡ መሪ ደግሞ ከሰማይ የሚወርድ ወይም ከመሬት የሚፈልቅ አይደለም፡፡ አንደዛማ ቢሆን ሀገራት (ኢትዮጵያን ጨምሮ) በየጊዜው ለሚያካሂዱት ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ባላባከኑ ነበር፡፡ መሪ ከሰዎች መካከል የሚታወቅ፣ ከመታወቅም በሰዎች ፈቃድ የሚሾም ነው፡፡ ይህ እውነታ ለኢትዮጵያ ሙስሊምም ይሠራል ብለን እናምናለን፡፡ ሕገ-መንግሥቱም በማያሻማ ቋንቋ አስቀምጦታል፡፡ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች መተዳደሪያ ደንብ መሠረትም ሕዝበ-ሙስሊሙ መሪዎቹን በየአምስት ዓመቱ በአደባባይ ይመርጣል፡፡ በአደባባይ የሚለው ቃል ይሰመርበት፡፡ (ለማንኛውም የምናወራው ንድፈ-ሀሳቡን (ቲዎሪውን) ነው፡፡ ምክንያቱም መሬት ላይ ካለው ነገር ይልቅ ንድፈ- ሀሳቦች ይበልጥ ያግባባሉ)፡፡ መሪ ተቀባይነት ሲኖረው በሁሉም መስክ ስኬታማ ሥራዎችን ማከናወን ይችላል፡፡ በተቃራኒ ከሆነ ያው ውጤቱም ያው ተቃራኒ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሁኔታ (ከታሪክ እንደምረዳው ሕዝቡ በነገሥታቱ በተከፋ ቁጥር የንጉሱን ባላንጣ እየደገፈ ነገሥታቱን ሲያባር ሥርዓታቸውንም መቃብር ቤት ሲሸኝ ኖሯል፡፡ ከዘመነ መሳፍንት በኋላ አብዛኛው ሀበሻ የወረሳቸው ልማዶች አሉ፡፡ ነገሥታቱ በቅርብ ዘመዶቻቸው ሳይቀር እየተመረዙ ሲሞቱ፤ መሳፍንቱ ሳይወዱ ግዳቸውን የቀረበላችውን ምግብና መጠጥ እፊታቸው እንዲቀመስ ማስደረግ ጀምረው ነበር- ጭንቀታቸው፡፡
ሙስሊሙ ህብረተሰብ ‹‹የኔ›› የሚለው መሪ ማግኘት ጥቅሙ ለሙስሊሙ ብቻ የሚመስለው ሰው ብዙ በመሆኑ ጉዳዩ ቸል ሲባል ሰንብቷል፡፡ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሙስሊሙ ከልቡ የሚያምንበት መሪ ሲያጣ ከጉዳቶች ሁሉ ትንሹን የሚጎዳው ሙስሊሙ ነው፡፡ ጉዳቱ በዋነኛነት አገራችንን በመቀጠል መንግሥት ከዚያ ሙስሊም ያልሆነውን ወገን በመጨረሻም ሙስሊሙን ይነካል፡፡ እያንዳንዱን በመጠኑ ለመቃኘት ያህል፡፡
የመጀመሪያ ተጎጂ-- ኢትዮጵያችን፡-
አዕምሮው ጤነኛ የሆነ ሁሉ እንደሚያውቀው ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን ናት፡፡ የዚህች ቤት (የኢትዮጵያ) ቋሚና ማገር፣ ግድግዳና ጣሪያ እኛው ነን፣ ሕዝቦቿ፡፡ ማናችንም፣ ከማናችንም ያነሰ ዋጋ የለንም፡፡ ያለ ቋሚው ግድግዳው፣ ያለግድግዳው ጣሪያው አይኖርም፡፡ ያለነዚህ ቤቷ የለችም፡፡ ወይም ያለ ሕዝቦቿ ኢትዮጵያ የለችም፡፡ ይህን እንደ መንደርደሪያ (platform) እንያዝና ጨዋታችንን እንቀጥል፡፡
ግድግዳው ከምር ‹‹ግድግዳ›› ካልሆነ ለስሙ ግድግዳ የተባለ ግዑዝ ቢቆም ፋይዳ የለውም፡፡ ይልቅስ አንድ ቀን ይወድቅና ጉድ ያፈላል፡፡ ቋሚም ‹‹ቋሚ›› መሆን አለበት፡፡ አለዚያ ሙሉ ቤቷን ይዞ ይተኛል፡፡ ቤት ማለት እንግዲህ የመዋቅሩ ጥንካሬ መታያ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የምንታይባት ፎቶአችን ናት፡፡ የአዲስ አበባን ጎዳናዎች የታዘበ ስለቆሻሻ ያለንን አመለካከት ያለማንም አስረጅነት ያውቃል፡፡ ለምን? አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ፎቶ ነችና፡፡
ወደ ቀደመው ወሬያችን እንምጣና፤ እንደግድግዳ ወይም እንደቋሚ የሚያገለግል የህብረተሰብ ክፍል ከልቡ የቤቱን (የሀገሩን) አስፈላጊነት አምኖበት ያለምንም ማልመጥ ሥራውን ባግባቡ ሊከውን ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊምም (የኢትዮጵያን አስፈላጊነት ማመኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ባይሆንም) መከፋት ሲበዛበት (ይሄን የሠይጣን ጆሮ አይስማው) የመሠረትነው ትዳር ይፍረስ፣ ሰማንያችን ይቀደድ ላለማለቱ ምን ዋስትና አለን?
መሪ የማጣት ስሜት የወላጅ አልባነት ስሜት አለው፡፡ ወላጅ የሌለው ሕፃን ትልቁ እጣው ቤት ጥሎ የጎዳና ተዳዳሪ መሆን ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የሚፈልጉ ወገኖች ሁሉ፣ የሀገሪቱ ሙስሊሞች የወላጅ አልባነት ስሜት ውስጥ እንዳንገባ መከላከል ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሁለተኛው ተጎጅ - መንግሥት፡-
የሀገራችን መንግሥት የ‹‹ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ መንግሥት›› ነትን ፍልስፍና የሚከተል መንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት ዋነኛ ሚና (በተለይም የፌዴራል መንግሥቱ) ሀገሪቱን በጠቅላላ ወይም የሁለትና ከዚያ በላይ ክልሎችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናል፡፡ በኛ ሀገር እውነታ እስልምና የሌለበት ክልል፣ ክርስቲያኖችም የማይገኙበት ክልል የለም፡፡ ስለዚህም የሀይማኖቶች ጉዳይ የፌዴራል መንግሥቱ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሥር የሀይማኖቶችና የእምነቶችን ጉዳይ የሚከታተል ዴስክ የተዋቀረ ነው፡፡
ሙስሊሙ እንደ ሕዝብ የኔ የሚለው መሪ ሲያጣ መንግሥት ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ ግቦቹን ለማሳካት ይቸገራል፡፡ ልማትም ሆነ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በሕዝቦች ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆን ለስኬታማነቱ የማይታለፍ ጉዳይ ነው፡፡ ያኮረፈ ሕዝብ በሙሉ ልቡ ለልማት አይነሳም፡፡ ተጎዳሁ የሚል ሕዝብ ገንቢ ሚና አይጫወትም፡፡
ሙስሊሙ መሪ (ወይም ከልቡ የሚያምንበት መሪ ልበል መሰለኝ) በማጣቱ ብቻ ሃገሪቱ ማግኘት የሚገባትን እጅግ ብዙ እሴቶች አጥታለች፡፡ እያጣችም ነው፡፡ ከልማት ጋር የተያያዘውን አንዱን ጉዳይ እንኳ ለማሳየት ያህል፡-
በኢትዮጵያ 35 ሚሊዮን ሙስሊም ቢኖር ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 5 ሚሊዮኑ ዘካተል ፊጥር የማይወጅብበት (ግዴታ የማይሆንበት) ቁርሱን በልቶ ምሳውን ለመድገሙ እርግጠኛ ያልሆነ ያጣ የነጣ፣ ሙልጭ ያለ ድሃ ቢሆንና የተቀረው ግን ቢያንስ የዛሬን እንኳ መመገቡን የሚያውቅ ቢሆን በትንሹ 30 ሚሊዮን ዘካተል ፊጥር የሚያወጣ ዜጋ አለ ማለት ነው፡፡ ይህ 30 ሚሊዮን ህዝብ፣ በነፍስ ወከፍ በአመት አንድ ግዜ ይበልጥ ድሃ ለሆኑ ሰዎች ሁለት ኪሎ ከግማሽ እህል ይሰጣል፡፡ የአንድ ኪሎ እህል(ገብስ ወይም ሥንዴ) ዋጋ 8 ብር ቢሆን አንድ ሰው በነፍስ ወከፍ 20 ብር ይከፍላል ማለት ነው፡፡ ሃያን በ30 ሚሊዮን ስታበዙት 600 ሚሊዮን ብር ታገኛላችሁ፡፡ ስለዚህ ለብዙ የሃገሪቱ ገበሬዎች በጣም በቀላሉ የ600 ሚሊዮን ብር ገበያ ተገኘ ማለት ነው፡፡
ይሄ እንግዲህ ዘካተል ፊጥር ብቻ ነው፡፡ በዘካተል ማል ደግሞ 85 ግራምና ከዚያ በላይ ወርቅን ያህል ሃብት ያለው ማንኛውም ሙስሊም በየአመቱ የሀብቱን 2.5% ዘካ ያወጣል፡፡ በሰሞኑ ገበያ የ24 ካራት ወርቅ ዋጋ 400 ብር አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ዘካተል ማል ግዴታ እንዲሆንበት 34 ሺህ ብር ሊኖረው ይገባል፡፡ 34 ሺህ ብር ያለው ሰው ደግሞ 850 ብር ዘካ ያወጣል፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ ከ35 ሚሊዮን ውስጥ 34 ሺህ እና ከዚያ በላይ ያለው ሙስሊም (ሃገሪቱ ሚሊየነር ገበሬዎችንም እያፈራች) እንደው አሳንሰን 4 ሚሊዮን ብቻ ነው እንበል፡፡ 4 ሚሊየኑ (የመጨረሻ ትንሹ 850 ብር ቢሆንም) በአማካይ 2 ሺ ብር ቢያወጣ፤ (2 ሺ በ4 ሚሊዮን ስታበዙት) 8 ቢሊዮን ብር ይመጣል፡፡ በድምሩ 8ቢሊዮን 6 መቶ ሚሊዮን ብር፣ መንግስት አምጡ ብሎ ሳይለፍፍ፣ ሳይቆጣና ሳያስፈራራ፣ መቆጣጠርያ ማሽን ሳይተክል፣ ፍርድ ቤቶችና ፖሊስ ስራ ሳይበዛባቸው ሊሰበሰብ ይችላል ማለት ነው፡፡
በሌሎች ሃገራትም ሆነ፣ በሙስሊሙ ታሪክ እንደሚታወቀው ዘካ ታማኝና ተቀባይነት ያለው መሪ እስካለ ድረስ በአንድ ማእከል ነው የሚሰበሰበው፡፡ 8.6 ቢሊዮን ብር ደግሞ በአንድ ማዕከል ቢሰበሰብ በኢትዮጵያ ምን ያህል ስራ ሊሰራ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ በቀደሙት ስርዓቶች መሪዎቻችን(መሪዎቻችን?) ሙስሊሙን ሲገፉት፣ ሲገፉት ኖረው ዛሬ መንግስት ከኢትዮጵያ አንፃር’ንኳ ኃላ ቀር የሚባሉ አምስት ክልሎችን ተረክቦ ልዩ ድጎማ እያደረገላቸው ይገኛል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ አራቱ ሙስሊም ብዙሃን የሆነባቸው ክልሎች ናቸው፡፡ በዚህ በየአመቱ ያለ ድካም በሚሰበሰብ 8.6 ቢሊዮን ብር በሃረር ስንት የውሃ ጉድጓድ ይቆፈራል? በአፋር ስንት ት/ቤት፣ በሱማሌ ስንት የጤና ኬላ ይከፈታል?
ሌላው ደግሞ ገንዘቡ፤ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያውን የሚሰበሰብ በመሆኑ፤ ሰሞኑን በበጎ አድራጎት ማኅበራት አዋጅ ምክንያት፣ መንግስትን ከማህበራቱና ከአንዳንድ ሃገራት ዲፕሎማቶች ጋር ሲያጨቃጭቀው የነበረው የ”ፈረንጅ ጣልቃ ገብነት” ስጋት መቶ በመቶ ይወገዳል፡፡
ለዚህ እንግዲህ ሙስሊሙ ሲጠራው አቤት፤ ሲልከው ወዴት የሚለው መሪ ያስፈልገዋል፡፡ በተጨባጭ የምናየው ግን እንኳንስና ቢሊዮን ብሮች፣ የበግ ቆዳ አምነው የሚሰጡት መሪ ጠፍቷል፡፡ በዚህም ምክንያት፤ሁሉም በግሉ ቅንጥብጣቢ ሣንቲም ለየግለሰቡ እየሰጠ፤ ለሃገር ልማትና እድገት መዋል የሚገባው ገንዘብ በየአመቱ ድህነት እያባዛ ይገኛል፡፡ ያሳዝናል፡፡
ሙስሊሙ እውነተኛና ታማኝ መሪ ሲያጣ መንግሥት አላስፈላጊ ኃይልና ጉልበት ማባከን ግድ ይለዋል፡፡ ምክንያቱም ስጀምር እንደተናገርኩት ነቢዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ሦስት ሰዎች እንኳ መንገድ ሲሄዱ መሪ እንዲመርጡ አዘዋል፡፡ የርሳቸውን ትዕዛዝ በተግባር ላይ ለማዋል መጣጣር ደግሞ የአንድ ሙስሊም፣ ሙስሊም የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ሰው ሙስሊም ለመባል በአላህ ብቸኛና እውነተኛ አምላክነት ከማመን ጎን ለጎን (ልብ አድርጉ ቀጥሎ አላልኩም) የነቢዩ መሐመድን(ሰ.ዐ.ወ) ነቢይነት መቀበል ይገባዋል፡፡
ከነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) ትዕዛዛት ውስጥ ደግሞ መሆን፣ መሪ መምረጥ አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ዋነኛ የሚባል በትክክል የሚታመንበት መሪ ሲጠፋ በየመንደሩ መሪዎች መፈጠራቸው አይቀርም፡፡ በዚህ መሀል ታዲያ፤ መንግሥት አንዴ ‹‹ኳሪጅ›› አንዴ ‹‹ምንትስ›› የሚላቸው አይነት ሰዎች መፈጠራቸው የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ ስለሆነም ከነዚህ ጋር በሚደረግ ሰዶ ማሳደድ ኃይል መባከኑ፤ ጉዳት መድረሱ ደአይቀርም፡፡
ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ መቼም ሕዝብ ጊዜ የሚያመጣቸውን ጥያቄዎች ማንሳቱ አይቀርምና፣ ኢትዮጵያዊው ሙስሊም የዚህ አይነት ጥያቄ በሚኖረው ጊዜ መንግሥት ማንን ሊያናግር ይችላል? ይኽን ሁሉ ኁልቁ መሳፍርት እንዴት ይቆጣጠረዋል? በመሆኑም መንግሥት በየትኛም አጋጣሚ ቢሆን ሙስሊሙም ሆነ ሌላው፣ መደበኛ የሆነ መሪ ባይኖረው ኢ- መደበኛ የሆኑ መሪዎችን መፍጠሩ የማይቀር ሀቅ መሆኑን በማወቅ፤ ኢ-መደበኛ መሪዎች ደግሞ ሊያደርሱ የሚችሉት ጥፋት የከፋ በመሆኑ፣ መንግስት ለሙስሊሙ ህብረተሰብ መደበኛና ‹‹የኔ›› የሚላቸው መሪዎች መፈጠር (ሕገ-መንግሥታዊ አጥሩ እንደተጠበቀ ሆኖ) ድጋፍ ሊያደርግ ይገባዋል የሚል እምነት አለ፡፡
አሁን በቅርቡ እንኳ በየጎዳናው ስናየው የነበረው መበሻሸቅና መፋጠጥ አጋፋሪዎቹ መደበኛ የተባሉቱ እንዳልነበሩ ሁሉም የታዘበው ነው፡፡
ሦስተኛ ተጎጂዎች - ሙስሊም ያልሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች፡-
በቅርቡ በሞት የተለዩን ታላቁ ኢትዮጵያዊ የሀገር ሽማብሌና ምሁር (በዴቪድ ላምብ አገላለጽ ቤተ-መጻህፍት) ሐጂ በሽር ዳውድ (አላህ ይዘንቸውና) የአይን ምስክር በተሰኘው እና በአቶ አብደላ አብደረህማን በጻፉት መጽሐፍ መግቢያ ከዚህ የሚከተለውን አስፍረዋል፡፡ (ሀሳቡን እንጂ ቃል በቃል አይደለም) ‹‹…. በቦታውም ሙስሊሙ ትምህርት ሳይማር የድንቁርና ቀንበር ተጭኖት ስላየሁ የአካባቢውን አስተዳዳሪ እቢሮው ሄጄ ለምንድን ነው ሙስሊሙን የማታስተምሩት?›› ብዬ ብጠይቀው በፍጥነት ሄዶ በሩን ዘጋውና አመልካች ጣቱን ከናፍሮቹ ላይ አድርጎ ‹‹እሽ! እሽ!›› አለኝ፡፡ ‹‹እኔ እንደሰማሁህ ሌላው እንዳይሰማህ›› …. ሙስሊሙ እንዳይማርና እንዲህ በዘላንነት እንዲኖር ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ እንዳለ እንዴት ጋዜጠኛ ሆነህ አታውቅም?” አላቸው፡፡ ሸህ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ እንዳሉት (እኔም እንደምለው) ‹‹አይሆንም፡፡ እኛ በድንቁርና ኋላ ቀርተን እናንተ ብቻችሁን ልትሠለጥኑ አትችሉም፡፡ ወደ ኋላ እንጎትታችኋለን፡፡››
አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም፡፡ አንዱ ለግሞ አንዱ እግር ብቻውን አይራመድም፡፡ ለዚች ሀገር ህልውና ሁላችንም እናስፈልጋለን፡፡ ሙስሊሙ በተከፋበት ሁኔታ ሙስሊም ያልሆነው ደስተኛ ሆኖ አይቀጥልም፡፡
የሙስሊሙ እውነተኛ መሪ ማጣት ሙስሊም ያልሆነውን ወገን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይመለከተዋል፡፡
በየሠፈሩ ከሚፈጠሩ ሺ ባላምባራሶች አስሩ እብሪተኛ ቢሆን ምናልባትም የተቀሩት ዘጠኝ መቶ ዘጠናዎቹ ከሚያለሙት በላይ ሊያጠፋ ይችላል፡፡ ሙስሊም ያልሆኑትን መተናኮል የኢስላም ባህሪ ባይሆንም ቅሉ፤ ይህ አይነት ባህሪ ያላቸው ቡድኖች እንዳይፈጠሩ ሙስሊም ያልሆኑት ወገኖችም ሊያሳስባቸው ይገባል፡፡ ከሙስሊሙ ጋር በመሆን ሙስሊሞች የሚያምኑበት መሪ፣ የሚታዘዙት አባት እንዲኖራቸው መታገል ይታያቸዋል፡፡
ሙስሊሞች ያልተባበሩበት ልማት፣ ሙስሊሞች ያላመኑበት እድገት ከቶ ሊፈጠር አይችልም፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ዛሬ የዓለም ሁኔታ ተቀይሯል፡፡ የምንፈራው ጽንፈኝነት እንዳይመጣ ሙስሊሙን እውነተኛውን የሠላም ጎዳና (ማለትም እስልምናን) የሚያመልክቱት ሰዎች ማግኘቱን ማረጋገጥ ይገባል፡፡
አራተኛው ተጎጅ -ሙስሊሙ ህብረተሰብ፡-
ቀደም ብዬ እንዳሰፈርኩት ሙስሊሙ ከልቡ የሚያምነው መሪ ቢያጣ ከሁሉም ያነሰውን ጣጣ የሚሸከመው ሙስሊሙ ነው፡፡ ምክንያቱም ታሪክ ምስከር ነው፡፡ እንኳንስና ዛሬ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊም፣ ድሮ እንኳ በአፄዎች ጊዜ አይደለም መሪ ማግኘት ስሙን እንኳ መግለጽ በማይችልበት ዘመን ኖሯል፡፡ ከመኖርም አልፎ እንደ ኑክሊየር ፊዥን እየሠፋ ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ ኢስላም በባህሪው ፍፁም ማዕከላዊ በሆነ ስርዓት (papal system) የግድ አያስፈልገውም፡፡
መሪ በዋናነት የሚፈለገው እንዲወክል ነው፡፡ ለመወከል ደግሞ መቶ ሺ ሰው በአስር ሺ ተወካዮች ተበታትኖ መቀጠል ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን ይህን ስል ሙስሊሙ ሙሉ አቅም ያላቸውና የሚያምናቸው መሪዎች በማጣቱ ለአንዲት ስንዝር ጉዳይ፣ መቶ ሜትር መጓዝ ሲኖርበት ሺ ሜትር እየተጓዘ መሆኑን ሳልክድ ነው፡፡
ማጠቃለያ
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በየትኛው መስፈርት ሲታይ ትልቅ ህዝብ ነን፡፡ ለኛ በትክክል ሀይማኖቱን የሚያውቁ፣ እኛም የምናውቃቸውና የምናከብራቸው እንጂ፣ ከመስጂዶች እንጂ፣ ከቂቤ በረንዳና ከቆዳ በረንዳ የመጡ መሪዎች አይገቡንም፡፡ አይመጥኑንም፡፡ ፈጽሞ ፡፡ እኛ ለኢትዮጵያ፣ሙስሊሞች በመሆናችን ምክንያት ብቻ፣ ልናበረክት የምንችላቸው ቁም ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ በአጭሩ ሙስሊሙ የወርቅ እንቁላል የሚጥል ዶሮ ማለት ነው፡፡ የወርቅ እንቁላል የምትጥለውን ዶሮ ደግሞ ማን ያርዳታል? (በዚህ ርዕስ ዙርያ መልሰን እንገናኝ ይሆናል-ኢንሻ አላህ)
Saturday, July 3, 2010
Subscribe to:
Posts (Atom)